የሲዳማ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ የቅርብ ጊዜ ዜናዎች
አንድነት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ ሀገር በማጽናት ለትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ አቅም መሆኑን ለማስረዳት ኢትዮጵያውያን ህያው ምስክር ናቸው።
የአንድነትን ምስጢር ከመተረክ ባለፈ የሀገራቸውን ዳር ድንበር፣ ታሪክና የተፈጥሮ ሀብት ለማስከበር ከሀገር በፊት በመሰዋት በተግባር ኖረውታል።
ትናንት ኢትዮጵያን ለማጽናት ከቅኝ ገዢዎች ጋር ተፋጠው በዓድዋ የድል ታሪክ አትመዋል፤ በኋላም የፋሺስት ጣሊያንን ዳግም ወረራ እምቢኝ በማለት በዱር በገደል ተዋድቀዋል።
እነዚህ ደማቅ ድሎች የዛሬው ብሎም የነገው ትውልድ በሀገሩ እንዲኮራ ከማድረግ የተሻገረ የአንድነትን ጉልበት በተግባር የገለጡ የታሪክ ምስክር ናቸው።
ኢትዮጵያ የትውልድ ድርሻቸውን በመወጣት ፈንታ ትናንትን ብቻ በማየት የተጠመዱ ዜጎች አይበጇትም፤ የዚህ ትውልድ ድርሻ ከትናንት በመማር፣ ዛሬ ላይ በመትጋት ለነገ የተሻለች ሀገር ማቆየት ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይህን የተገነዘበ ሀገራዊ ርዕይ ተሰንቆ ኢትዮጵያን በቀጣናው ብሎም በአህጉሪቱ የብልጽግና ምልክት ለማድረግ ብዙ ርቀት መጓዝ ተችሏል።
ኢትዮጵያ በዋዛ ፈዛዛ የተነጠቀቻቸውን ታሪካዊና ስትራቴጂያዊ ሀብቶቿን ለማስመለስ የጀመረቻቸው የዲፕሎማሲ ጥረቶች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ማግኘት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
ይህ ትውልድ እነዚህ መልካም ጅምሮች ፍሬ አፍርተው ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት በማድረግ ረገድ በቀደምት አባቶቹ የህይወት መስዋዕትነት የተረከበው አደራ አለበት።
ትውልዱ አደራውን እና የዜግነት ድርሻውን በወጉ እንዲወጣና ከዳር ድንበር ሉዓላዊነት ባሻገር በኢኮኖሚ ጫና ያልጎበጠች ሀገር ለነገ ለማቆየት የሚችልበትን ቁልፍ ጭምር መውረሱን ልብ ይሏል።
ይህ ቁልፍ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር ለባዕዳን የማትንበረከክ ጠንካራ ሀገር ለልጆቹ ለማውረስ በጎሳና በሀይማኖት፤ በብሔርና በመደብ ሳይለያይ በአንድነት የመቆም ኃይል ነው።
ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሀገራቸውን ከማጽናት ባለፈ ለአፍሪካውያን የነጻነት ተጋድሎ አርዓያ ሆነዋል፤ ውቅያኖስ ተሻግረው በደም መስዋዕትነት ለወዳጅ ሀገራት ጋሻ ሆነዋል።
ኢትዮጵያ የምታነሳቸው የብሔራዊ ጥቅም ጥያቄዎች የህልውና ጉዳይ በመሆናቸው ከመንግስት የዲፕሎማሲ ርምጃዎች ባሻገር የሕዝቦቿን አንድነት በጽኑ ትሻለች።
ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ከፍታ በአንድነት መቆማቸው የሚኮሰኩሳቸው አንዳንድ የውጭ ኃይሎች የሁለንተናዊ ብልጽግና ጉዞዋን ለማደናቀፍ የሚገለገሉባቸው የውስጥ ባንዳዎች እዚም እዚያም ሲፍጨረጨሩ ይስተዋላል።
ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል ጠላቶቿን ድል እየነሳች ጸንታ የዘለቀችው ባንዳዎች ስላልነበሩ ሳይሆን የሕዝቧን የአንድነት ገመድ መበጠስ ስላልተቻላቸው ነው።
አበው "ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው" እንዲሉ፥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተመዘገቡ አስደናቂ ለውጦችን የካደ አሉባልታ በመንዛት ሕዝቡን ከልማት ለማናጠብ የሚኳትኑ አካላት ተበራክተዋል።
ሕዝቡ እኚህ የባዕዳን ተቀላቢ ባንዳዎች በተለያዩ መንገዶች ለሚያሰራጩት መሰረተ ቢስ ወሬ ጆሮ ሳይሰጥ አንድነቱን አጥብቆ በጀመረው የልማት መንገድ መጓዝን መርጧል።
የኢትዮጵያ መጪ ዘመናት ባዕዳን እንደደገሱላት የጥፋት ምኞት ሳይሆን በሕዝቧ ከአለት የጠነከረ አንድነት ጸንታ በከፍታ የምትታይበት እንደሚሆን መላው ኢትዮጵያውያን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያሳዩት ቁርጠኝነት እማኝ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን በምርጫው የነበራቸውን ተሳትፎ በማውሳት "ተዓምረኛ ሕዝብ" በማለት መግለጻቸውም ሕዝቡ የአንድነትን ኃይል በቅጡ መረዳቱን የሚያጠይቅ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፥ "የዳበረ ባህል፣ እጅግ ሀገር ወዳድና የወል መሻቱን መጠበቅ የሚችል ሕዝብ መሆኑን በዘንድሮው ምርጫ ዳግም ለዓለም አሳይቷል" ነበር ያሉት።